ጌትነት  አያናው

 

Click here to edit subtitle

<ነቢዩ ኤልያስ> በአራት ኪሎ


 click here to download in pdf
ሰሞኑን በከተማችን በአዲስ አበባ ‹ነቢዩ ኤልያስ መጥቷል፣ የዓለምም ፍጻሜ ቀርቧል› የሚሉ አካላት ተነሥተዋል፡፡ እነርሱ እንደሚሉትም ነቢዩ ኤልያስ መጥቶ አዲስ አበባ ይገኛል፡፡ ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ክህነቱን ለማጥራትም ተዘጋጅቷል፡፡ ከሚያጠራቸው የቤተ ክህነት ጉዳዮች ሦስቱ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ የመጀመርያው ‹ኦርቶዶክስ የሚባለው ስም ስሕተት ነው፤ ስማችን ተዋሕዶ ነው፤ መለበስ ያለበት ልብስ ነጭ ብቻ ነው፤ እርሱም ቢሆን ጥለቱ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ መሆን አለበት፤ አሁን ያደረግነውን ማተብ በመበጠስም አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ማተብ ማሠር አለብን› የሚል ነው፡፡ በየአጋጣሚው ቤተ ክህነቱንና ቤተ መንግሥቱን በመንቀፍ፣ አሁን የሚታዩትን ችግሮች መሠረት አድርጎም ሕዝቡ መጥቷል የተባለውን ኤልያስ መከተል እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዱ ጥቅም እንደሌለው እየተነገረው ነው፡፡ የሚከናወኑ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም የኤልያስን መምጣት የሚያመለክቱ እንጂ ምእመናኑ ሊሳተፍባቸው የሚገቡ አለመሆናቸው ይነገራል፡፡
እስኪ እነዚህን ነገሮች በዝርዝር እንያቸው፡፡
ኤልያስ ማነው?

ኤልያስ ማለት ‹እግዚአብሔር አምላክ ነው› ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው መክዘ አካባቢ በእሥራኤል የተነሣ ነቢይ ነው፡፡ የተወለደው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ይገኙ ከነበሩት የገለዓድ ቀበሌዎች በአንዱ በቴስቢ ነው፡፡ ኤልያስ የሚታወቀው በሦስት ሃይማኖታዊ ተግባሮቹ ነው፡፡ የመጀመርያው በእሥራኤል ተንሰራፍቶ የነበረውን የበኣል አምልኮ ያጠፋና አምልኮ እግዚአብሔርን ያጸና መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አሕዛባዊቷን ኤልዛቤልን አግብቶ ንጉሡ አክአብ ይፈጽመው የነበረውን ግፍና ጥፋት ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት የገሠጸና ለእውነት ብቻ የቆመ ነቢይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አቋሙ ምክንያትም በሰሜናዊ እሥራኤል በሚገኙ ሰንሰለታማ ተራሮች ፈፋ ለፈፋ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ መጀመርያ ቁራዎች ሲመግቡት ኖረው በኋላም በሰራፕታ የምትገኝ አንዲት መበለት አገልግላዋለች፡፡
ይህ ቆራጥነቱና ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቋሚ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ባስገኘለት ሞገስ የተነሣ ኤልያስ ከኄኖክ ቀጥሎ ሳይሞት ወደ ብሔረ ሕያዋን በመወሰዱም ይታወቃል፡፡ የዮርዳኖስን ወንዝ ከደቀ መዝሙሩ ከኤልሳዕ ጋር ከተሻገረ በኋላ የእሳት ሠረገላ መጥቶ ኤልያስን ወስዶታል፡፡ ይህ ኤልያስ የሚታወቅበት ሦስተኛው ነገር ነው፡፡
ኤልያስ ይመጣል?
ከ470 እስከ 440 በኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገረው ነቢዩ ሚልክያስ ‹‹የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ›› ብሎ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ (ሚል. 4÷5) ይህንንም በመያዝ አይሁድ በፋርሶች፣ በግሪኮች፣ በሶርያውያንና በሮማውያን መከራ በተፈራረቁባቸው 400 ዓመታት ውስጥ ነቢዩ ኤልያስን ሲጠባበቁት ነበር፡፡ በየምኩራባቸውም የኤልያስ መንበር የተባለ ከፍ ብሎ የተሠራ ባለ መከዳ ወንበር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ከክርስቶስ ልደት 6 ወራት ተቀድሞ የተወለደውና ከበረሃ የመጣው መጥምቁ ዮሐንስ በብዙ መልኩ ኤልያስን ይመስለው ስለነበር የተወሰኑት የአይሁድ ክፍሎችና በኋላም ክርስቲያኖች ይመጣል የተባለው ነቢዩ ኤልያስ እርሱ ነው ብለው ተቀብለውታል፡፡
ዮሐንስ መጥምቅ እንደ ኤልያስ ሁሉ በርኸኛ ባሕታዊ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ፀጉር የለበሰ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ እሥራኤል ተስፋ በቆረጠችበት ዘመን የመጣ ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ሄሮድስን ሳይፈራና ሳያፍር የገሠጸ ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስለው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይመጣል የተባለው ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን መስክሮለታል (ማቴ 11÷14፤ 17÷10-13፤ሉቃ 1÷17)
ስለ ኤልያስ መምጣት የሚነግረን ሌላው መጽሐፍ የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በምእራፍ 11 ላይ ዓለምን የሚያጠፋው ሐሳዌ መሲሕ ከመጣ በኋላ ዙፋኑን አደላድሎ የዓለምን ክርስቲያኖች ሲጨርስና ምስክር ሲጠፋ ሁለት ምስክሮች መጥተው 1260 ቀናት ምስክርነት እንደሚሰጡና በመጨረሻም በሐሳዌ መሲህ እንደሚገደሉ ይገልጣል፡፡ ከሁለተኛው መክዘ ጀምሮ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁለት ምስክሮች ኄኖክና ኤልያስ መሆናቸውን ተርጉመዋል፡፡
ሐሳዌ መሲሕ ሲነሣና ሁሉንም እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ሲያጠፋ፤ ለእውነት የሚመሰክርም ሲጠፋ፣ ምእመናንም በሚደርሰው መከራ ምክንያት የሚከተሉት የእምነት መንገድ ‹ስሕተት ይሆንን?› ብለው ሲጠራጠሩ እነዚህ ሁለቱ ሳይሞቱ ወደ ብሔረ ሕያዋን ያረጉ ነቢያት መጥተው እውነትን በመመስከርና የሐሳዌ መሲሕን ነገር በማጋለጥ ምስክርነታቸውን በደም እንደሚያጸኑ የሊቃውንቱ ትርጓሜ ያብራራል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አቡሊዲስ ዘሮምና ቪክቶርያነስ እንደሚገልጡት ኤልያስና ኄኖክ በኢየሩሳሌም ያስተምራሉ፣ በኢየሩሳሌም ተአምራት ያደርጋሉ፣ በኢየሩሳሌም ይገደላሉ፣ በኢየሩሳሌም ይነሣሉ፣ በኢየሩሳሌምም ያርጋሉ፡፡ ይህም ለጌታችን መምጣት የመጨረሻው ምልክት ነው፡፡ ከኤልያስና ኄኖክ መምጣት በኋላ የሚጠበቀው የክርስቶስ ለፍርድ መምጣት ነው፡፡
‹ነቢዩ ኤልያስ› በአራት ኪሎ›
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ነቢዩ ኤልያስ መጥቷል ይባላል፡፡ የሚኖረውም አራት ኪሎ ነው፡፡ አንዳንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች በተለይም አርቲስቶች ተከታዮቹ ሆነናል ይላሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከሊቃውንቱ ትምህርት ጋር ስናነጻጽረው ትክክል ሆኖ አናገኘውም፡፡
መጀመርያ ነገር ኤልያስ ብቻውን አይመጣም፡፡ በነቢዩ በሚልክያስ ለብቻው እንደሚመጣ የተነገረለት ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሰከረ ሌላ ምስክር ማምጣት አያስፈልግም፡፡ በሌላም በኩል አሁን መጥቷል የተባለው በመጨረሻው ዘመን የሚመጣው ኤልያስ ከሆነ ደግሞ እንደ ሊቃውንቱ ትምህርት ብቻውን አይመጣም፤ አብሮት ኄኖክም ይመጣል፡፡ አሁን ግን ኤልያስ ከኄኖክ ተነጥሎ ነው መጣ የሚባለው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ነቢዩ ኤልያስ የሚመጣበት ጊዜ በራእየ ዮሐንስ ላይ በምእራፍ 11 ተገልጧል፡፡ አስቀድሞ ሐሳዌ መሲሕ ይመጣል፡፡ ዙፋኑንም በተቀደሰችው ከተማ በኢየሩሳሌም ይዘረጋል፡፡ ምእመናንም (በተለይም የስድስት ስድሳ ስድስትን አምልኮ ያልተቀበሉትን) በግፍ ይገድላቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ እውነት ትቀጥንና ምስክር ታጣለች፤ ኤልያስና ኄኖክ የሚመጡትም እውነትን በአደባባይ ለመመስከር ነው፡፡
ይህ ከሆነና በአዲስ አበባ እየተባለ እንዳለው ኤልያስ ከመጣ ሐሳዌ መሲሕ ቀድሞት መጥቷል ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ምእመናን በግፍ ተገድለዋል፤ በዓለምም ላይ አማኞች በአብዛኛው አልቀዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲፈጸም አላየነውም፡፡ በኢየሩሳሌምም ሐሳዌ መሲሕ ገና አልነገሠም፡፡
ሌላም ሦስተኛ ነገር መነሣት አለበት፡፡ ሐሳዌ መሲሕ የሚነግሠው፣ ኄኖክና ኤልያስም የሚገለጡት ‹በተቀደሰችው ከተማ› በኢየሩሳሌም ነው፡፡ የሚሠውትም እዚያ መሆኑን ‹እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለችው ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት› ብሎ ኢየሩሳሌም መሆንዋን ነግሮናል፡፡ (ራእይ 11÷8) አሁን ግን ኤልያስ ተገለጠ እየተባለ ያለው አዲስ አበባ አራት ኪሎ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተልዕኮውም ከመጽሐፉም ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ጌታ የተሰቀለው አራት ኪሎ ነው ካላልን በቀር፡፡  
ራእየ ዮሐንስ እንደሚነግረን ኄኖክና ኤልያስ ምስክርነት የሚሰጡት ለ1260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት ወይም ለ ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይገደላሉ፣ ተነሥተውም ያርጋሉ፡፡ አሁን ግን አዲስ አበባ መጣ የተባለው ኤልያስ መጣ ከተባለ አራት ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡
ምጽአትንና መሲሕን መናፈቅ
በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምጽአትን ቀን የመናፈቅና የምጽአትን ምልክቶች ደርሰዋል ብሎ የመጨነቅ አዝማሚያ የሚከሰትባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ እነዚህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲከሰቱና ሕዝብ ተስፋ ሲቆርጥ ነው፡፡
እሥራኤላውያን ከፋሶችና ከግሪኮች ወረራ በኋላ ሀገራቸው ስትመሰቃቀል፣ መንፈሳዊነት ሲጎድልና መንግሥታቸው ፈርሶ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሲመጡ ‹መሲሕ እየመጣ ነው፤ ኤልያስ እየደረሰ ነው› የሚል አስተምህሮን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ2ኛው መክዘ ጀምረው ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንድ ሰዎች ይመጣል የተባለው መሲሕና ኤልያስ እኛ ነን እያሉ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሞክረው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛውና አንደኛው መክዘ ላይ የተነሡት ቴዎዳስና ይሁዳ ይጠቀሳሉ፡፡ ቴዎዳስ አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሐሰተኛ መሆኑ ሲታወቅ ሕዝቡ ተወው፤ ይሁዳም ሕዝቡን አስነሥቶ እስከ ማስሸፈት ደርሶ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን አላማረም፡፡ (የሐዋ 5÷37-38)
በቅርብ ጊዜ በኡጋንዳ ኢኮኖሚው ሲደቅና የእርስ በርስ ጦርነቱ ሲባባስ፣ ይህም የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወት ሲያቃውሰው ‹እኔ ክርስቶስ ነኝ› የሚል ሰው ተነሥቶ በአንድ አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ተከታዮቹ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲሉ በእሳት ተቃጥለው እንዲያልቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ በአሜሪካ የደረሰው የኢኮኖሚ ድቀት ካስከተላቸው መዘዞች አንዱ በየአካባቢው ‹እኔ መሲሕ ነኝ› የሚሉና ሕዝቡ ችግሩን ከማሸነፍ ይልቅ ችግሩን እንዲረሳው የሚያደርጉ ሰዎች መከሰታቸው ነው፡፡ በ2012 የተደረገ አንድ ጥናት ባለፉት ሦስት ዓመታት በአሜሪካ ውስጥ 132 ሰዎች መሲሕ ነን ብለው ተነሥተው ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ አስከትለዋል፡፡
በሀገራችን ታሪክ በ15ኛው መክዘ ከተከሰተው የግራኝ ጦርነት በኋላ ሕዝቡ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋ መቁረጥ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጠሉ፣ ኢኮኖሚው ወደመ፤ መንግሥቱ ተዳከመ፤ ትዳርንና አካባቢያዊ መስተጋብርን የመሰሉ ማኅበራዊ ተቋማት ፈረሱ፡፡ ብዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ ይህ በሕዝቡ ላይ ባስከሰተው ተስፋ መቁረጥ የተነሣ ከዚህ መከራና ሰቆቃ የሚያወጣውን አንዳች ሰማያዊ ኃይልን ይጠብቅ ነበር፡፡
በሀገራችን ታሪክ ራእየ ዮሐንስ ይበልጥ የታወቀውና በገልባጮች እጅ በብዛት የተገለበጠው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በሚሠሩት አብያተ ክርስቲያናትም የሐሳዌ መሲሕ፣ የኤልያስና ኄኖክ፣ የአዲሲቱ ሰማይና ምድር ሥዕሎችም በብዛት ተሳሉ፡፡ ይህንንም መሠረት አድርገው እነ ፍካሬ ኢየሱስ ተጻፉ፡፡ ፍካሬ ኢየሱስ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉትን ትንቢታዊ ቃሎች መሠረት አድርጎ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ያዛመደ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ ሕዝቡን ከችግር የሚያወጣ፣ የአንድ በሬ እሸት የአንዲት ላም ወተት እንዲያጠግብ የሚያደርግ ‹ቴዎድሮስ› የሚባል ንጉሥ ይነግሣል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ሕዝቡም በደረሰው ነገር ላይ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይህንን ቴዎድሮስ የተባለ ደግ ንጉሥ እንዲጠብቅ አደረገው፡፡
ከግራኝ ጦርነት በኋላ በዐፄ ሠርጸ ድንግል ወራሾች መካከል በተፈጠረው የርስ በርስ ውጊያ ሀገሪቱ ስትታመስና ሕዝቡም በተደጋጋሚ ጦርነትና የሕዝብ ፍልሰት ሲታወክ እኔ ክርስቶስ ነኝ፣ ሕዝቡንም ከችግሩ ላወጣውና መንግሥተ ሰማያትን ላወርሰው መጥቻለሁ የሚል ሐሳዊ መሲሕ በአምሐራ ሳይንት አካባቢ ተነሥቶ ነበር፡፡ አሥራ ሁለት ሐዋርያት፣ 72 አርድእትና 36 ቅዱሳት አንስትንም መርጦ ነበር፡፡ ብዙው ሕዝብም በተስፋ መቁረጥ ላይ ስለነበር ተከትሎት ነበር፡፡ በኋላ ግን በሞት መቀጣቱን አቡነ ጎርጎርዮስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡
በቅርቡ የሀገራችን ታሪክ ዐፄ ምኒሊክ ዐርፈው ሞታቸው በተደበቀበት ጊዜ፣ በታኅሣሥ ግርግር ጊዜ፣ በአብዮቱ ዋዜማና ማግሥት፣ እንዲሁም ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በገባበት ጊዜ አያሌ ‹ባሕታውያን› ተነሥተው ነበር፡፡ ይህ ነገር መጣ፣ መርስኤ ኀዘን ስለ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን በጻፉት የትዝታ መጽሐፋቸውም ይህንን ገልጠውታል፡፡ ይህም ያም ነገር ታየ፣ ተገለጠ የሚለው ብሂልም ነባርና የሀገር አለመረጋጋትና በኑሮ ተስፋ መቁረጥን ተገን አድርገው የሚመጡ ናቸው፡፡
የኤልያሳውያን› ሁለት አስተምህሮዎች
አሁን በዘመናችን የተከሰቱት ‹ኤልያሳውያን› ሁለት ነገሮች ላይ አተኩረው እየሠሩ ነው፡፡ የመጀመርያው ‹ኦርቶዶክስ› ትክክለኛ ስም አይደለም የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰንደቅ ዓላማን ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ማያያዝ ናቸው፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን ›ኦርቶ› ርቱዕ፣ ‹ዶክሳ› ደግሞ እምነት፣ መንገድ፣ ጠባይ፣ ባህል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስም የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት መጠቀም የጀመሩት በ325 ዓም ከተደረገው የኒቂያ ጉባኤ በኋላ ነው፡፡ ከጉባኤ ኬልቄዶን የ451 ዓም ጉባኤ በኋላ ደግሞ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ካቶሊክ ሲባሉ ምሥራቆቹ ‹ኦርቶዶክስ› የሚለውን ስም ይዘው ቀሩ፡፡ በምሥራቆቹ መካከል የጉባኤ ኬልቄዶንን ውሳኔ በመቀበልና ባለመቀበል መካከል ልዩነት ስላለ የግሪክና መሰል አብያተ ክርስቲያናት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ሲባሉ፣ አርመን፣ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ሶርያና ኢትዮጵያ ደግሞ ‹ኦርየንታል ኦርቶዶክስ› ተባሉ፡፡
ኦርቶዶክስ፣ ኦርቶዶክሳዊ የሚለው ስም በሀገራችን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሁለት መንገድ ተገልጠዋል፡፡ በአንድ በኩል ጥሬ ቃሉ እንዳለ የተቀመጠ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ግእዙ ተተርጉሞ ‹ርቱዕ ሃይማኖት› እየተባለ ተቀምጧል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ‹ይኩን ምእመነ ኦርቶዶክሳዌ› ይላል(42÷2)፡፡ ያዕቆብ ዘእልበረዲም ‹ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት› ሲል እምነቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፈ ቄርሎስም ‹ሃይማኖት ርትዕት› እያለ ተርጉሞ ይገልጠዋል፡፡
‹ተዋሕዶ› የሚለው ቃል ነጥሮ የወጣው በጉባኤ ኤፌሶን በ431 ዓም ነው፡፡ በጉባኤው የንስጥሮስን ባሕል ለማየት የተሰበሰቡት አበው በእስክንድርያው ቄርሎስ የተሰጠውን ትምህርት በመቀበል ሁለት ባሕርይ የሚለውን አውግዘው መለኮት ከሥጋ ተዋሕዶ ሥግው ቃል ሆነ የሚለውን ርቱዕ እምነት መሆኑን መሰከሩ፡፡ ይህ ቃል የእምነት መግለጫ ዶክትሪን ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላም ይህ ስያሜ የኦርቶዶክሶቹ ዋና መጠርያ እየሆነ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ መጻሕፍት ላይ ተዋሕዶ እምነት ሆኖ እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጠርያ ሆኖ አናገኘውም ‹ኦርቶዶክሳዊ› የሚለውን ቃል የምናገኘውን ያህል ‹ተዋሕዶዊ› የሚል መገለጫ አናገኝም፡፡ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል በነገረ ሥጋዌ ትምህርት ላይ በአጽንዖት እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ትምህርት ላይ በሀገር ውስጥ የተነሣ የተለየ አስተያየት ስላልነበር መጠርያነቱ አልጎላም፡፡
በ17ኛው መክዘ ከአውሮፓ በመጡ ካቶሊካውያን ምክንያት የተፈጠረውን የእምነት ክፍፍል ተከትሎ ይህ የእምነት መጠርያ የአማንያንና የወገን መጠርያ እየሆነ መጣ፡፡ በ17ኛው መክዘ ቅባትና ጸጋ የሚባሉ ባህሎች መጥተው ነበር፡፡ እነዚህን ባህሎች የሚቃወሙትና ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ እንጂ የጸጋ ልጅ አይደለም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት ከሥጋ በተዋሕዶ ሥግው ቃል እንጂ እንደ ነገሥታትና ነቢያት በመቀባት አይደለም ያሉት ደግሞ መጠርያቸው ከእምነታቸው ተወስዶ ‹ተዋሕዶዎች› ተባሉ፡፡ ከቦሩ ሜዳ ጉባኤ በኋላም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ስም ‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ› የሚለው ጎላ፡፡
ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለም የምትታወቅበት የወገን ስሟ ነው፡፡ ሌሎቹም ‹የግብጽ ኦርቶዶክስ› የሶርያ ኦርቶዶክስ› የሕንድ ኦርቶዶክስ› ብለው ይጠሩና ከአካባቢያቸው ራሳቸውን ለመለየት ደግሞ ‹የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ‹፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ፣ የሶርያ ያዕቆባዊት ኦርቶዶክስ› እያሉ ይጠራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ‹ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ› ትባላለች፡፡
አንዳንድ ሰዎች በዘመናውያን መዛግብተ ቃላት ስለ ‹ኦርቶዶክስ› የተሰጡ ፍቺዎችን ይዘው ይሞግታሉ፡፡ ኦርቶዶክስን ‹ከአክራሪነትና፣ ከለውጥ አለመቀበል› ጋር እያዛመዱ ይፈቱታል፡፡ በዚህም ምክያት ኦርቶዶክስ የሚለውን ቃል ለኮንሰርቫቲቭ ፓርቲዎችና አይሁድ ሲሰጡት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ከመነጨበት ጠባይ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡
አሁን ወደ ሁለተኛው ነጥብ እንመለስና ሰንደቅ ዓላማን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን መለያ ናት፡፡ ለዚህች ሰንደቅ ዓላማ ብዙዎች ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ እነዚህ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉት መካከልም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ልጆች ይገኙበታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክን ከማቆየት፣ ባህልን ከማሸጋገርና ኢትዮጵያዊነትን ከማሥረጽ ሚናዋ አንጻር ሰንደቅ ዓላማንም በማስከበርና ለትውልድ በማስተላለፍም የበኩልዋን ድርሻ ተወጥታለች፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ከሀገራዊ እሴትነቱ፣ መሥዋዕትነትንና ነጻነትን ከማንጸባረቁ፣ ለኢትዮጵያውያንም ከደማቸው ጋር የተዋሐደ ልዩ ምልክት ከመሆን አልፎ ግን ጽድቅና ኩነኔ ውስጥ የሚገባ፣ እርሱን ያልተቀበለና ያላደረገ ሰማያዊ ዋጋ የሚቀርበት፣ ከእርሱ ውጭ ቀለም ያለው ነገር የለበሰና ማተብ ያሠረ ኃጢአት እንደሠራ ተቆጥሮ ንስሐ የሚገባበት ግን አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለ ዜጋ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ለመሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና መቀበልን እንጂ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራን መቀበል ግዴታው አይደለም፡፡ በኡጋንዳ ባንዴራ፣ በአሜሪካ ባንዴራ፣ በግብጽ ባንዴራ፣ በሶማልያ ባንዴራ አሸብርቆም ቢሆን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጅ መሆን ይችላል፡፡ እስካሁን ስለ ቀኖና በሚደነግጉት መጽሐፎቻችን ውስጥ ሰንደቅ ዓለማን የተመለከተ ቀኖና የለንም፡፡
በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር እንጂ ከኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ጋር የታሪክ እንጂ የድኅነት ተዛምዶ የለውም፡፡
እንደዚህ ዓይነት አመለካከቶች የሚያይሉት እንዲሁ አይደለም፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ኢትዮጵዊ ስሜት ደብዝዟል፣ ለሰንደቅ ዓላማና ለሀገራዊ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል ተብሎ ሲታሰብ ሰንደቅ ዓላማን የመሰሉ ሀገራዊ እሴቶች ጉልበት ያገኙ ዘንድ ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ኃይል ይሰጣቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ትርጉም ማስተማርዋና በትውልዱ ውስጥ ማሥረጽዋ ባልከፋ፡፡ አስተምህሮው ግን ከሀገራዊ ግዴታ የሚመጣ እንጂ ከሃይማኖታዊ ግዴታ የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ከሕዝብ እሴቶች እንደ አንዱ ሆኖ እንጂ ከጽድቅና ኩነኔ ጋር ተያይዞ መሆን የለበትም፡፡
ምን ይደረግ?
የሃይማኖት ትምህርት በሚገባ መሰጠት ሲያቆምና ሰዎችም በተደላደለው የእምነት መንገድ ላይ በዕውቀትና በእምነት እየተመሩ መጓዝ ሳይችሉ ሲቀሩ ‹ባለ ተስፋዎች› ብቻ ይሆናሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ መጀመርያ ላይ ‹በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን› በማለት የገለጠው አባባል ታላቅ ነገር አለው፡፡ ምእመናኑ በሁለት ዓለም መኖራቸውን እንዳይረሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ‹በክርስቶስና በኤፌሶን›፡፡ ክርስቲያኖችም ምድራዊነታቸውንም ሰማያዊነታቸውንም መርሳት የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ምድራዊው ጎዳና ሲያቅትና ፈተና ሲበዛበት፣ የኢኮኖሚውና የፖለቲካውም ሁኔታ አልቃና ሲል፣ የምናየውና የምንሰማውም ተስፋ ሲያሳጣን፣ ምድር ላይ መሆናችንን ፈጽመን ረስተን ኅሊናችን ወደሚፈጥረው ልዩ ዓለም እንገባለን፡፡ ያንንም እጅግ ከመመኘታችን የተነሣ የደረስንበት ይመስለናል፡፡
በዚህ ጊዜ የሚሰጡ ትምህርቶችም ለሰዎች ቀላል የሆኑ፣ ንባብና ትምህርትን የማይጠይቁ፣ በቀላሉ የሚተገበሩ፣ የሚነኩና የሚዳሰሱ ይሆናሉ፡፡ ቡና መጠጣት አለመጠጣት፣ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ማተብ ማሠር አለማሠር፣ በባዶ እግር መሄድ አለመሄድ፣ ጸጉርን ማስረዘም አለማስረዘም፣ መቁጠርያን ያለ ሥርዓቱ ማሠር አለማሠር፣ ከመምህራን ቃል ይልቅ የሰይጣንን ቃል መቀበልና ማመን፣ እየሠለጠኑ ይመጣሉ፡፡
ለዚህ ትልቁ መፍትሔው የእምነት ተቋማት የራሳቸውን ሥራ (ወንጌል ማስተማርን )ትተው በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ስለዚህም ተቋማቱ መጀመርያ ራሳቸውን ወደ ተልዕኳቸው መልሰው፣ በማይጨበጥ ተስፋ የሚዋልለውን ሕዝብም ወደ ትክክለኛ ኑሮና ተስፋ መመለስ አለባቸው፡፡ እዚህ ኤልያስ ነኝ፣ እዚያ ድንግል ማርያም ነኝ፣ እዚያ አቡዬ ነኝ የሚሉ በተነሡ ቁጥር ሕዝቡ ሥራና ትዳር ፈትቶ ተንከራትቶ አይዘልቀውም፡፡

ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም፥ ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ።አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ።በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።ምዕራፍ 62:1-3
መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች።መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።ሉቃ 1፤28-30 መልአኩ ገብርኤል እንዳመሰገናት እኛስ ብናመሰግናት ብንዘምርላት ክብራን ለ አለም ብንመሰክር ስተታቺን ምኑ ላይ ነው ?
ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። የሉቃስ ወንጌል 1:41-45
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።መዝሙረ ዳዊት 87:5
ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ።መዝሙረ ዳዊት 129:5
የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።ትንቢተ ኢሳይያስ 60:14

ነቢዩ ኤልያስ በአራት ኪሎ

from daniel kibret

ይሕ ፖስት ፪ ኣመት በፊት ፖስት የተደረገ ነው ማለተም ፪፻፬ ላይ

getnet ayanaw